Upcoming Event:
 • 00

  days

 • 00

  hours

 • 00

  minutes

 • 00

  seconds

Upcoming Event:

 • 00

  days

 • 00

  hours

 • 00

  minutes

 • 00

  seconds

ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን (ወንጌላዊ አማኝ)

ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን (ወንጌላዊ አማኝ)

ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን (ወንጌላዊ አማኝ)

ክርስቲያን ነኝ የሚል ሁሉ ክርስቲያን ነውን? ቤ/ክ የሚለውን ስም የተሸከመ ሁሉ የክርስቶስ አካል  ነውን?  ከየትኛው ቤ/ክ ወይም ከየትኞቹ አማኞች ጋር ነው መንፈሳዊ ሕብረት ማድረግ የምንችለው? እኛ የምንዘምረውን መዝሙር ከሚዘምር ሁሉ ጋር ወይም ኢየሱስ ኢየሱስ ከሚለው ሰው ሁሉ ጋር ወይም መጽሐፍ ቅዱስን እዚህና እዛ ጋር ከሚጠቅሰው ሁሉ ጋር መንፈሳዊ ሕብረት ማድረግ እንችላለን?

ከኛ በፊት የቀደሙት አባቶቻችንና እናቶቻችን ከኦርቶዶክስ ቤ/ክ የወጡት በዛ የነበሩት መሪዎች ስላሳደዱቸው ብቻ ነው ወይስ መንፈሳዊ ሕብረት ማድረግም ስላቃታቸው? ወንጌላውያን አማኞችን ወይም ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ክርስቲያን ነን ከሚሉት የሚለየን ምንድነው? ከኦርቶዶክስ፣ ከካቶሊክ ወይም አሁን በየቦታው እየተከፈቱ ካሉት ምን ይለየናል?  እነዚህና እነዚህን የሚመስሉ ጥያቄዎች አሁን ባለንበት ዘመን በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ የሚጉላሉና መመለስ የሚገባቸው ናቸው።

ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ስም ሁሉ ስለሚጠቀምበት ልዩነታችንን ማወቅ አስፈላጊ የሆነበት ዘመን ላይ ነን። ማንነታችንን ማወቅ ሌሎቹን ለመመዘንና ከአንዳንዶቹ ጋር ደግሞ ህብረት ለማድረግም ላለማድረግም ይረዳናል።

ከኛ መካከል በወጡ ግን ብዙ ነገራቸው እንደኛ ባልሆኑ ሰዎች የወንጌሉ መልዕክትና የቤ/ክ መልክ እየተበላሸ/ እየተዥጎረጎረ ያለበት ዘመን ነው። ይሄ በኛ ዘመን ብቻ የሆነ አዲስ ነገር አይደለም። በተለያየ ዘመን፥ በተለያየ ስፍራና በተለያየ መንገድ ሃስተኞች ተነስተዋል (ይነሳሉም)። ቤ/ክ.ም እነዚህን ስትጋፈጥ ኖራለች (ትኖራለችም)።

ሐዋርያው ጴጥሮስ በመልዕክቱ 2ኛ ጴጥሮስ 2፡1-3 ላይ ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም” ብሏል።

እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ትምሕርት ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች በኛ መካከል ነው የሚኖሩት፣ የሚያጠፋ ኑፋቄን እኛ መሃል ነው የሚያስገቡት፣ ብዙዎችም የሚከተሏቸው ከኛው መሃል ነው፣ የሚሰደበውም እኛ የምንከተለው የእውነት መንገድ ነው።

ሐዋ. ዮሐንስ በ1መጀመሪያው መልዕክቱ ም.2 ላይ ይሄ የመጨረሻው ዘመን ነው ካለ በኋላ በመሃከላቸው ስለተነሱ ሃሰተኞች ሲናገር “ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ” ይላል።

ታዲያ አንድን አማኝ ወንጌላዊ አማኝ ወይም አንዲትን አጥቢያ ቤ/ክ ወንጌላዊት ቤ/ክ እንድንል የሚያደርጉን መሠረታዊ ትምህርቶች (እሴቶች) ምንድን ናቸው? እንደ ወንጌላዊ አማኝ እያንዳንዳችን ልናውቃቸው የሚገቡ መሰረታዊ እውነቶች አሉ። እነኝህ መሰረቶች ከሌሉ መንፈሳዊ ሕብረት ከሰውም ከቤተ ክርቲያንም ጋር ማድረግ አስቸጋሪ ነው። እነዚህ እውነቶች ወንጌላውያን አብየተ ክርስቲያናትን ከቀደሙትም አብያተ ክርስቲያናት ወይም አሁን በየቦታው ከሚከፈቱት ይለየናል። ሁሉም (እኛንም ጨምሮ) በዚህ መመዝን አለብን።

 • የቃሉ ስልጣን፦ Biblicism – 2.ጴጥ. 1፡20-21 ፣ 2.ጢሞ. 3፡16

“ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”

ወንጌላውያንን አንዱ ልዩ የሚያደርገን ለቃሉ የምንሰጠው ቦታ ነው። ቃሉ በሁሉ ቦታ ከሁሉ በላይ ባለስልጣን ነው እንላለን። ከቃሉ በላይ ታሪክም፣ ባህልም፣ መሪዎችም፣ ልምምዶችም መገለጦችም መሆን አይችሉም ብለን እናምናለን። ሁሉ በቃሉ ይመዘናል/ ይመረመራል/ ይፈተናል፤ ቃሉ ግን በማንም አይመዘንም/ አይመረመርም/ አይፈተንም። በዚህ አንደራደርም።

የቤ/ክ ተሃድሶ የመጀመሪያ መፈክራቸው “ቃሉ ብቻ” የሚል ነበር። ያ መፈክር ዛሬም አይለወጥም። ቃሉ ብቻ ለህይወታችን መመሪያ ነው፣ መልስ ነው፣ መሪ ነው፣ ፈዋሽ ነው፣ ስህተት የሌለበት ነው፣ ፍጹም ነው፣ ሙሉ ነው። በዚህ አቋም ብዙዎች ተሰደዋል፣ መከራ ተቀብለዋል፣ ተገድለዋል።

ቃሉ ባለስልጣን ካልሆነ በግልም እንደ ተቋምም የእምነት አንድነት (ህብረት) ልናደርግ አንችልም። ቃሉ የበላይ ባለሥልጣን ባልሆነበት ቦታ ሁሉ አማኞቹም ቤተ ክርስቲያኗም ወንጌላዊት ሊባሉ አይችሉም። ከወንጌላዊት ቤ/ክ እና እምነት ወጥተዋልና።

 • የክርስቶስ መስቀል፦ Crucicentrism– 1.ቆሮ. 2፡2 ፣ ገላ. 3፡1

“በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና”

ሌላው ወንጌላውያን አማኞችን ልዩ የሚያደርገን የመስቀሉ መልዕክት ነው። የመስቀሉ መልዕክት የሌለው የወንጌል አገልግሎት ምሰሶ የሌለው ቤት ማለት ነው፤ አይቆምም ይናዳል/ ይፈርሳል። የወንጌሉም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱሳችን መካከለኛውና ዋነኛው መልዕክት የክርስቶስ መስቀል ነው።

ነቢያት የተነበዩለት፣ ክርስቶስ የኖረበት/ የሆነበት፣ ሐዋርያት ያመለከቱት ሁሉም ወደ መስቀሉ ነው።

እምነታችንን ልዩ የሚያደርገው ጌታችን ያስተማረው ትምህርትና ተዓምራቱ ሳይሆን በመስቀል ላይ የሰራው የቤዛነት ስራና ትንሣኤው ነው። ለዚህ ነው ጌታ የመጣበትን ተልዕኮ ሲናገር በማቴ. 20፡28 ላይ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ያለው። መስቀል የሽንፈት የውርደት ምልክት አይደለም።

ኢየሱስ በርግጥ ተዋረደ እኛ ግን በሱ ከበርን፣ እሱ ተፈረደበት እኛ ግን ከፍርድ ነጻ ወጣን፣ ኢየሱስ ተጨነቀ/ ተሰቃየ እኛ ግን ሰላምን አገኘን፣ እሱ ተገረፈ/ ቆሰለ እኛ ግን ተፈወስን፣ እሱ በመስቀል ላይ ሞተ እኛ ግን ሕይወትን አገኘን፣ ኢየሱስ የተሸነፈ መሰለ እኛ ግን በሱ ከአሸናፊዎች በለጥን።

ይሄ የመስቀሉ ቃል ከኛ ፊት ከጠፋ ስተናል/ ጠፍተናል ማለት ነው። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ የገላትያን አማኞች 3፡1 ላይ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” ያላቸው።

ብልጽግና፣ ጤንነት፣ መባረክ፣ ባህል፣ ስርዓት . . . መስቀሉ ከሸፈኑት ይሄ ጤነኛ ወንጌል አይደለም/ ጤነኛ ክርስትና አይደለም። ይህ ከወንጌላውያን አማኞች ትምህርትና እምነት ያፈነገጠ ነው።

 • ዳግም መወለድ (የሕይወት ለውጥ)፦ Conversionism – ዮሐ. 1፡12-13 ፣ ዮሐ. 3፡3

ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።”

ወንጌላውያን አንድ ሰው ወንጌሉን ሰምቶ፣ በክርስቶስ አምኖ፣ ንስሃ ገብቶ፣ ዳግመኛ ተወልዶ፣ የእግዚአብሔር ልጅነት ስልጣን ተቀብሎ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ይሆናል፤  ሕይወቱ ሁሉ ይለወጣል ብለን እናምናለን።  ለወንጌላውያን አማኞች ከተዓምራት ሁሉ የሚበልጠው ትልቁ ተዓምር ይህ ነው።

ንስሃ የሌለበት፣ የሕይወት ለውጥ የሌለበት፣ ለክርስቶስ መገዛት የሌለበት፣ ቅድስና የሌለበት ድነት የለም። ድነት በጅምላ አይደለም። አንድ ሰው በግሉ ከአምላኩ ጋር መገናኘትና መለወጥ አለበት። እውነተኛ ሪቫይቫል የህዝብ ብዛት ሳይሆን የህይወት ለውጥ ነው።

ሌሎች ተዓምራቶችን ሁሉ ሴጣን ሊያደርጋቸው ይችላል፤ ዳግም መወለድና የህይወት ለውጥ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የሚሆኑ ብቻ ናቸው። ይሄንን የማታስተምርና የማትለማመድ ቤ/ክ እና ይሄንን የማያምንን አማኝ ወንጌላውያን ናቸው ብለን ለመጥራትና ሕብረትን ለማድረግ አስቸጋሪ ነው።

 • አማኝ የመንፈስ ቅዱስ መኖሪያ፦ The Lordship of the Holy Spirit – ዮሐ. 14፡16-17 ፣ ዮሐ. 2፡20

“እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።”

ሌላው ወንጌላውያን አማኞችን ልዩ የሚያደርገን አማኝ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው የሚለው ጽኑ አቋማችን ነው። ፓ/ር ሃይሉ ቸርነት ይሄንን ሲያስተምር “አንድ አማኝ መንፈስ ቅዱስን ወደ ህይወቱ ሲጋብዝ ነዋሪ መሆኑ ቀርቶ መኖሪያ ይሆናል” ብሏል። ጌታችንም ያለን የሚመጣው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችሁ ይኖራል ነው።

ስለዚህ ቅቡዓን የሚባሉት ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ አማኞች ሁሉ ከቅዱሱ ቅባት ተቀብለናል/ ተካፍለናል ብለን እናምናለን። መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ህይወት ውስጥ ሲኖር ደግሞ እሱን ይመራዋል፣ ያስተምረዋል፣ ያበረታዋል። የአማኙ ህይወት ያድጋል፣ ይቀደሳል፣ ፍሬ ያፈራል፣ ያገለግላል፣ ለውጥ ይታይበታል።

መንፈስ ቅዱስ የመጣው በውስጣችን ሊኖር፣ ወደ እውነት ሁሉ ሊመራንና ክርስቶስን እንድንመስል ሊያደርገን ነው እንጂ ሊያንጫጫንና አንዳንድ ትሪኮችን ሊያሳየን ወይም ከሰው ሁሉ የተለዩ ሰው ሁሉ ሊሰማቸውና ሊያዳምጣቸው የተገቡ ልዩ ሰዎችን ሊቀባ አይደለም። ይሄ ከወንጌላውያን አስተምሮ ውጪ ነው።

ከሰው ሁሉ የተለየው ሰው፣ ሰዎች ሁሉ ሊሰሙት፣ ሊከተሉት፣ ሊያምኑት የተገባው በመንፈስ ቅዱስ የተቀባው የቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ጥቂት ሰዎችን ወይም ልምምዶችን ወይም ትምህርቶችን ወይም ባህልን ከሁሉ በላይ አጉልቶና ለይቶ የሚያሳይ ትምህርትና አቋም ከወንጌላውያን አማኞች ትምህርትና እምነት የወጣ ነው።

 • ቤተ ክርስቲያን፦ Church as a Community

ቤ/ክ ስንል ህንፃው ሳይሆን ክርስቶስ ራስ ሆኖ ቅዱሳን በህብረትና በአንድነት የሚኖሩበት የአማኞች ስብስብ እንደሆነ ይገባናል። ስለዚህ ቤ/ክ አማኞች በህብረት ሆነው የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚለማመዱበት፣ ህይወታቸው የሚታነጽበት፣ የሚጠበቅበትና የሚያድግበት፣ ለወንጌልም ሥራ የሚዘጋጁበት የክርስቶስ አካል ናት።

ወንጌላውያን አማኞች እንደዚህ ያምናሉ። አካሉ/ ሙሽራው ነችና ልናከብራትና ልንጠነቀቅላት ይገባል።  ቤ/ክ እኛ እንደፈለግን የምንወጣባትና የምንገባባት፣ የምንነቅፋትና የምንደፍራት አይደለችም።

አካሉን የሚገነጣጥሉ፣ ህዝቡን የሚያተረማምሱ፣ ለመንጋው ምንም የማይራሩ እነኝህ ወንጌላውያን አማኞችን አይወክሉም።

 • የአማኝ እንቅስቃሴ፦ Activism – ማቴ. 25፡31-40

የመጨረሻው ወንጌላውያን አማኞችን መለያችን “አማኞች በቃልና በስራ በህብረተሰቡ ውስጥ መገለጥ አለባቸው” የሚለው አቋማችን ነው። የወንጌል አማኞች በህብረተሰቡ ውስጥ ወንጌልን በቃል በማወጅ (በመመስከር) ደግሞም ያላቸውን በማካፈል (ጉልበታቸውን/ ጊዜያቸውን/ ገንዘባቸውን በማካፈል) ወንጌልን በህይወታቸው ይኖሩታል።

ወንጌል በስራ የሚለው ነገር ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ በእግዚአብሔር ፍቅር የሚደረግ አገልግሎት ነው እንጅ (NGO) አይደለም። የተራበን ማብላት፣ የታመመን መጎብኘት፣ የተቸገረን መርዳት፣ የታሰረን መጠየቅ . . . የወንጌል አንዱ ተልዕኮ ነው። ከዚህ እምነት የተነሳ ነው Salvation Army, Red Cross, World Vision የመሳሰሉት በወንጌላውያን አማኞች የተጀመሩት።

ወንጌላውያን አማኞች አካሉ እንዳለ በቃልና በተግባር ለወንጌል አገልግሎት መንቀሳቀስ አለበት ይላሉ። ስለዚህ የወንጌል አገልግሎት የአካል አገልግሎት ነው እንጂ አንድ ሰው ጎልቶ የሚታይበት፣ ወይም በሳምንት 1 ቀን ብቻ አብረን የምንተያይበት አይደለም። ህብረተሰቡ ውስጥ ተጽዕኖ ማምጣት አለብን።

እነኝህ 6 መመዘኛዎች ካንድ አማኝ ወይም ቤተ ክርስቲያን ጋር ሕብረት ለማድረግ መመዘኛዎቻችን ናቸው። ማንም ሕብረት አድርጉ ስላለን አናደርግም ወይም አታድርጉ ስላለን እንሸሽም። በመጀመሪያ እኛም ሆንን ያለንበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወንጌላውያን እንደሆንን መፈተሽ ተገቢ ነው።

እነዚህ ስናደርግ ግን እኛ ሐሰተኞችን ስንጠብቅ በራዕይ ምዕራፍ 2፡1-7 ላይ እንደ ተጠቀሰችው የኤፌሶን ቤ/ክ ፍቅራችን እንዳይቀዘቅዝ መጠንቀቅ አለብን። ጌታ ኢየሱስ የኤፌሶንን ቤ/ክ ስለ ጥንቃቄዋ ሲያመሰግናት ግን የቀድሞ ፍቅሯን ስለጣለች በቀፋት።

“ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ፦ ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤ … ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና።  እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ።

ራሳችንንም ሆነ ቤተ ክርስቲያንን ስንጠብቅ ንጹሁም ወንጌል እንዳይበረዝ ከሃሰተኞች ጋር ስንጋደል የመዳናችን ደስታ (ፓሽን) እንዳይጠፋብን፣ የመን/ቅ ስጦታዎችን ቸል እንዳንል ይልቁንም በየቀኑ በመንፈስ የምንቃጠል እንድንሆን አሳስባችኋለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may use these HTML tags and attributes: <a href="" title=""> <abbr title=""> <acronym title=""> <b> <blockquote cite=""> <cite> <code> <del datetime=""> <em> <i> <q cite=""> <s> <strike> <strong>