Upcoming Event:
  • 00

    days

  • 00

    hours

  • 00

    minutes

  • 00

    seconds

Upcoming Event:

  • 00

    days

  • 00

    hours

  • 00

    minutes

  • 00

    seconds

ከተልዕኮ በክርስቶስ ማመን ይቀድማል!

Post

ከተልዕኮ በክርስቶስ ማመን ይቀድማል!

ከተልዕኮ በክርስቶስ ማመን ይቀድማል!

ድሆችን ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ አይጠቅመኝም። 1 ቆሮ 13:3

ከላይ የተጠቀሰውን  የመ/ ቅዱስ  ክፍል ስንመለከት ሐዋሪያ ጰውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ከልግስናም ሆነ በመንፈሳዊ ስጦታ አገልግሎት የሚቀድመው ፍቅር እንደሆነ የገለጸበት ክፍል ነው። በእርግጥ የክፍሉ አውድ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን የተከሰተውን መከፋፈል፣ የተዘበራረቀ የጸጋ ስጦታ አጠቃቀምና የአማኞችን ባሕሪና አለመቀደስን ለማረምና ለማስተካከል የተጻፈ ነው።

በአንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13ን ስናነብ ብዙ ጠቃሚ ነጥቦችን እንመልከታለን። ሰው ያለ ፍቅር ለጋስ ወይም መንፈስዊ ስጦታ ሊኖረው ይችላልን? በዚህ ክፍል ፍቅር የተባለው ማን ነው? ብላችሁ ራሳችሁን ከጠየቃችሁ የእግዚአብሄር ቃል ሕይወታችሁን እንዲያነባችሁ ፈቅዳችኋል ማለት ነው።

ምንም እንኳን የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የዚህን ክፍል አውድ መተንተን ባይሆንም በግርድፉ የሐዋሪያ ጳውሎስን ሃሳብ ስንረዳ በአጭሩ ሰው ያለፍቅር መሰዋዕት ሊሆን ወይም ያለውን ሁሉ እስከመስጠት ሊደርስ እንደሚችል ያሳየናል። በዚህ ክፍል በጉልህና በሚታይ ደማቅ ጽሑፍ ለሁሉም አንባቢ በግልጽ የሚያሳየው ማንም ሰው ድርጊቱ (የሕይወት መሰዋዕትነትም ሆነ በጎ አድራጎት) ምንጩ ወይም ወይም መሰረቱ ፍቅር ሊሆን ይገባል የሚል ነው። ከፍቅር ውስጥ ያልወጣ ወይም ፍቅር ያላስገኘው ድርጊት በእግዚአብሔር ሚዛን ከንቱ ነው። ክፍሉ የሚነግረን ሰው ፍቅር ሲኖረው ድርጊቱም ሆነ ፍሬው በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት አለው። በሌላ አነጋገር ከፍቅር ውጪ ፍሬያማ ድርጊት ወይም እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ የሆነ ሥራ ሊሰራ አይችልም። ፍቅር ማነው? ለሚለው ጥያቄ በግልጽ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ባይገለጽም ይህ ፍቅር ሰማያዊና መለኮታዊ ነው። ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ ሲያምን በአማኙ ልብ ውስጥ የሚፈስ የእግዚአብሔር ፀጋ ነው። ይህ በክርስቶስ በማመን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ፍቅር ክብሩን ለእግዚአብሔር የሚሰጥ፣ በራሳችን እንዳንመካ የሚያደርግ፣ በመሰጠት እንድናገለግል ራሳችንን ሳይሆን ኢየሱስን ለሌሎች እንድናሳይ የሚያደርግ ነው። ከዚህ ውጪ የሆነ ተልዕኮ፣ ድርጊት፣ አገልግሎት እንዲሁም ችሮታ በእኛና ለእኛ ማንነት ዙሪያ የሚያጠነጥን፣ ጌታን የሚሸፍን፣ እኛን የሚያጎላ ምድር ምድር የሚሸት ይሆናል። ለዚህ ነው ማዘር ትሬዛ እንዲህ ያሉት፦ “ምን ያህል መስጠትህ ሳይሆን በምትሰጠው ስጦታ ውስጥ ምን ያህል ፍቅር መኖሩ ነው ትልቁ ነገር” ብለዋል።

ይህ ጹሑፍ ተልዕኮን ስናስብ የሚረዳውም ሆነ ተረጂው ልብ ውስጥ ሊታይ የሚገባው ክርስቶስ እንደሆነ ያመለክተናል። የሚረዳው (በጎ አድራጊው) በክርስቶስ ፍቅር ሲያደርገው ተረጂው ክርስቶስን ያከብራል። ከዚህ የተነሳ የየተኛውም ተልዕኮ ግቡ ኢየሱስን ማሳየት ሊሆን ይገባል። በሰብዓዊነት ሰዎችን መርዳት የተገባና ማንም ሊያደርገው የሚገባ ሰናይ ምግባር ነው። በዓለም ላይም ከዚህ የተነሳ በግብረ ሰናይነታቸውና በበጎ አድራጎት ሥራቸው የተመሰገኑ ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ብዙ ድርጅቶች አሉ። ሆኖም ሰው በጎ አድራጊዎችም ሆነ በጎ ነገር የተደረገላቸው፣ የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነውን ይህንን ፍቅር /ክርስቶስን/ ካላወቁት ከንቱ ነው። ለዚህ ነው ኢየሱስ “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?” ያለው። ሰው ሁሉ ያለውን የመስጠት አቅም ቢኖረው ኢየሱስ ከሌለው አልያም የኢየሱስን ፍቅር ለሌሎች መስጠት ካልቻለ ሕይወት ትርጉም የለውም። ተቀባዩም ሁሉን ተቀብሎ ክርስቶስን ካላገኘ ዘላለማዊ ለውጥ በሕይወቱ አይመጣም። ከላይ ያነሳናቸውን ሃሳብ በግልጽ ሊያስረዳ የሚችል የአንድ ታላቅ መንፈሳዊ ሰው ሕይወት ታሪክ እስቲ እናንብብ።

ይህ ሰው ጆን ዌስሊ ይባላል። ይህ ሰው ለአምስት ዓመት በኦክስፎርድ ሴሚናሪ የተከታተለ ሲሆን ለአስር ዓመት በቸርች ኦፍ ኢንግላንድ አገልግሎአል። በአገልግሎቱ መጨረሻ  እ.ኤ.አ በ1735  አካባቢ ሚሸነሪ በመሆን ከእንግሊዝ ወደ ጆርጂያ ሄደ። በዚያ በጆርጂያ በነበረው አገልግሎት ከፍተኛ የሥራ ውጤት ለማግኘት በመጓጓት ነበር የሚያገለግለው። ሆኖም ይበልጥ ተስፋ መቁረጥ፣ ባዶነት፣ እንዲሁም ጭንቀት ሕይወቱን አናወጠው። ከጥዋቱ 4 ሰዓት ሲሆን ይነሳና ይጸልያል፣ ለአንድ ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስ በየቀኑ ያነባል። ከዚያም ወደ እሥር ቤት በመሄድ እሥረኞችን ያጽናናል፣ ወደ ሆስቲታል በመሄድ ህመምተኞችን ይጎበኛል። ሌሎች በተለያየ ችግር ሲያልፉ ይረዳል ይጸልይላቸዋል። ዌስሊ ይህንን ለብዙ ጊዜ አደረገ ሆኖም አገልግሎቱ የውስጥ እርካታና ዕረፍት ሳይሆን ጭንቀትና የማይገፋ ሥራ ሆነበት።

ከዚህ የተነሳ ከአሜሪካ ወደ እንግሊዝ ለመመለስ ወሰነ። ከዚያም ወደ እንግሊዝ በመርከብ ሲመለሱ ታላቅ የባሕር ማዕበል በመነሳቱ የነበሩበት መርከብ ተናወጠች፣ ልትሰጥም ጀመረች። ንፋሱ የመርከቡን አካል እየመታ ማፍረስና መገነጣጠል  ጀመረ፣ ከዚህ የተነሳ ዌስሊ እጅግ ፈራ። ፍርሃቱ እየጨመረ ሲሄድ እንደሚሞት ሲያስብ በእጅጉ ፈራ። ቢሞት ምንም ዋስትና እንደሌለው በማሰብ በብርቱ ደነገጠ። ከላይ እንደተገለጸው ዌስሊ ብዙ ያገለገለና መልካም ሥራ የሰራ ቢሆንም ሞትን እጅግ የሚፈራና በፍጹም ሊያስበውም የማይፈልገው ነገር ነበር።

በዚያ ጭንቅ ውስጥ እያለ እርሱ ከነበረበት መርከብ ትይዩ ሌሎች የክርስቲያን ሚሺነሪ ቡድኖች በዚህ ጭንቅ ውስጥ ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ ተመለከተ። ማዕበሉ ካለፈ በኋላ ዌስሊ እነኚህ የተለወጡ ክርስቲያኖችን፣ መርከባቸሁ ሲናወጥ በዚህ ጭንቅ ውስጥ እንዴት ሳትደነግጡ ትዘምራላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም እንደዚህ ብለው መለሱለት፦ “ይህ ያለንበት መርከብ ወደ ውስጥ ቢሰጥም እኛ ደግሞ በክብር ወደላይ እንደምንሄድ ዕርግጠኖች ስለሆንን ነው ብለው መለሱለት።” እርሱም እንዲህ በልቡ እንዲህ አለ፦ እኔ ሌሎችን ልለውጥ ሄድሁ፣ እኔን ግን ማን ይለውጠኝ? አለ።

በእግዚአብሄር እርዳታ መርከብዋ በብዙ ነውጥ አልፋ እንግሊዝ ገባች። ዌስሊ እዚህ ከደረሰ በኋላ ወደ Alderigate Street Chapel ወደምትባል አነስተኛ ቤተክርስቲያን ሄደ። በዚያም ቁጭ ብሎ መልዕክት ሲያዳምጥ፣ አንድ ሰው ከ200 ዓመት በፊት በማርቲን ሉተር የተጻፈውን (Luther’s preface to the book of Romans) ስብከት በዚያ ያለው አገልጋይ ሲያነብ በተመስጦ ያደምጥ ነበር። የመልዕክቱ ዋና ሃሳብ አጉልቶ የሚናገረው እውነተኛ እምነት ምን ዓይነት እንደሆነ ነበር። በክርስቶስ ብቻ ማመን ያድናል…በራሳችን ሥራ ልንድን አንችልም የሚል ነበር። ዌስሊ ይህን መልዕክት ከሰማ በኋላ ራሱን ሲመለከት ከዚህ ቀደም የያዘው የሃይማኖተኛነት መንገድ ትክክለኛ መንገድ እንዳልሆነ በሚገባ ተገነዘበ። በዚያን ምሽት የሚከተለውን ቃላት በማስታወሻው ላይ፦ “አሁን ከምሽቱ ዘጠኝ ሰዓት ነው። ልቤ በደስታ ሞቀ፣ በእርግጥ በክርስቶስ ሥራ ብቻ እንደዳንኩ በውስጤ ተሰማኝ፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞቱ ለደህንነቴ ብቁ እንደሆነ አመንኩ፣ ሃጢያቴ በደሙ እንደታጠበልኝ፣ ክርስቶስ ከሕግ፣ ከፍርድ እና ከሃጢያት ባርነት ነጻ እንዳደረገኝ እና ፍጹም ደህንነት እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆኛለሁ።” የሚል ጽሑፍ ጻፈ። ከላይ ያለውን ታሪክ ስታነቡ ሰው ሳይለወጥ ሊያገለግል ይችላልን? ብላችሁ ከጠየቃችሁ የዌስሊ ታሪክ ለጥያቄው ትክክለኛ መልስ ይሰጣል። በክርስቶስ ሆነን ስንሰጥ ክብሩን ጌታ ይወስዳል የሚረዱትም ጌታን ያያሉ።

ከዚህ ቀደም ስለነበረው ሕይወት ዌስሊ ሲናገር እምነቴ፣ ትምህርቴ፣ እውቀቴ፣ ድካሜ ሁሉ በምሰራው ሥራ ላይና  በራሴ ላይ ያተኮረና የተመረኮዘ ነበር። በክርስቶስ የመስቀል ሥራ ላይ ከመደገፍ ይልቅ ዌስሊን ነበረ የበለጠ የማምነው ብሏል። ከዚህ እውነተኛ ለውጥ በኋላ ብዙ ፍሬያማ የሚሺነሪ ጉዞ ከማድረጉም ባሻግር የ18ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ስባኪ፣ የሚቶዲስት ቤተክርስቲያን መስራች እንዲሁም በርከት ያሉ የቤተክርስቲያን አሰራሮችንና የስነመለኮት እውነቶችን ለወንጌል አማኞች ማህረሰብ አበርክቶአል።